Total Pageviews

Wednesday, July 17, 2013

"ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ!"


በአንዲት ገጠር ከተማ የሚኖር አንድ ሰው ነበር አሉ፡፡  
ሰውየው መቃብር እየፈነቀለ ትኩስ አስክሬን አየጎተተ አውጥቶ መልሶ ይቀብራል፡፡ ግን ደግሞ የለበሱትን ልብስ ያጌጡበትን ጌጥ የደረቡትን ኩታ እያወጣ ይዘንጥበታል፡፡

ለዚህ ሰው የአንድ የአከባቢው ሰው ሞቶ እናም ተቀበረ ማለት ሀዘን ሳይሆን የደስታ ምንጭ ሆነ፡፡ ሰው ይሞታል ይቀበራል እሱም ሬሳውን አውጥቶ ልብሱንና ጌጡን ገፎ መልሶ ይቀብራል፡፡ ህዝብ ተማረረ፡፡ የፍትህ ያለ ቢልም መፍትሄ የሚሰጥ ጠፋ፡፡

መቸም ሰው ሆኖ ከአፈር የሚቀር የለምና ይህ ነውጠኛ ህዝብን ያስነባ ሰውም ተራው ደርሶ ሞተ፡፡ ፌሽታው በተራው የህዝቡ ሆነ፡፡ የአከባቢው ሰው ሆ ብሎ ደስታውን ለመግለፅ በነቂስ ወጣ…ስለቴ ሰመረ ያለ ፤ ወደ ፈጣሪው ያንጋጠጠም ብዙ ነበር፡፡ የሀዘን ሳይሆን የሰርግና ምላሽ ቀን መሰለ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ በሚያየው ነገር ያዘነና የተቆጨ አንድ ሰው  ነበር፡፡ እሱም የሟቹ ብቸኛ ወንድ ልጅ ነው፡፡
                        
                   ልጅ የአባቱን ስም በመልካም ሊያስጠራ ዛተ፡፡ ጭካኔው ግን ከአባቱ ከፋ፡፡

የተቀበረ አሰክሬን እያወጣ የፈለገውን ይወስዳል አስክሬኑን ሳይመልስ እንኳ ባለበት ጥሎ የሄዳል፡፡ ተቀበሩ የተባሉት ሰዎች አስክሬን አመሻሽ ላይ በጅብ እየተጎተተ የተለያየ  የሰውነት ክፍላቸውም ከነዋሪው ደጅ ላይ ሁሉ ይጣል ጀመረ፡፡ ሕዝብ እግዚኦ ፈጣሪ ምኑን ላከብን ሲል ኡኡታውን አለ፡፡ ኧረ አባቱ በምን ጣዕሙ እሱው ይሻል ነበር ቢያንስ እሬሳውን መልሶ አፈር ሳያለብስ አይሄድም ነበር ተባለ፡፡

                                ልጅ ዝቶም አልቀረ፡፡ አባቱን አስመሰገነ፡፡

ጡረታ የወጣሁ መምህር ነኝ ያሉ አንድ አባት ናቸው ያጫወቱኝ፡፡ አሳቸው የፈለጉትን ጉዳይ ለማስረዳት ተጠቀሙበት እኛ ደግሞ በታሪክ ፈረስ ጋልበን ዛሬ ላይ እንምጣ፡፡

ኢትዮጲያ በተለያየ ስርዓት እና  መንግስታት ስር አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ የስርዓትም ባይሆን በየግዜው የተለያዩ አዳዲስ የወንበር ለውጦች መደረጋቸውን ይሰማል ይታያልም፡፡ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር አይተናል፡፡ ከሰሞኑ እንኳ ወሬው ሁሉ ሹመትና ሽረት ሆኗል…አዳዲስ ሚንስትሮች ፤ አማካሪዎች ፤ ከንቲባ ሌላም ሌላም፡፡

ስልጣኑን በሙስና ተዘፍቋል ተብሎ የተነጠቀ አለ፡፡ በአቅም ማነስ ፤ ከአንዱ ወደ አንዱ ለማገለባበጥ ታስቦ የተነሳ እና ቦታ የቀየረም አለ፡፡ ስራ ዘመኑን አጠናቆ የተሰናበተም አለ፡፡ ለኛ የማይታይ ምክንያትም ይኖር ይሆናል፡፡

እገሌ ሄዶ እገሌ ቢመጣም በአንድ ነገር እንግባባለን ፤ ህዝብ ሁሌም ከትላንት የተሻለውን ለዛሬው ይመርጣል፡፡ ይገባዋልም፡፡
የባሰበት ደም መጣጭ ርሃብተኛ አያ ጅቦ ሌቦ ቦጥቧጭ ፤ ከእጅ አይሻል ዶማ የሆነ የአቅም ውስንነት  ያለበት የሚሰራውን በውል የማይችል አስተዳዳሪ ከሆነ ተመስገን ሳይሆን የትላንቱን አምጡልኝ ያስብላል፡፡ገና ምን አየህ ተብሎ ለእንካ ቅመስ እጅጌ መሰብሰብም ነገ ያስተዛዝበናል፡፡

አዳዲሶች መሪዎቻችን ከቀደምቶቹ ስህተት ሊማሩ እና ሊያርሙ ይገባል እንጂ መሳ ለመሳ በፈሰሱበት ሊፈሱ አይገባም፡፡ የሱ ወይም የሷ ግዜ ተብሎ የምንዘክርላቸው አዲስ ሃሳብ አዲስ አሰራር አዲስ ለውጥ እንዲያሳዩን ከወዲሁ እጃችሁ ከምን ብለናል፡፡

ጥሎብን ይሁን ተጥሎብን ባላውቅም ዘመናችን ዝምታ ያይልበታል፡፡ ወንበር የሰጠናቸው ሰዎች ግን ንግግራችንን ብቻም ሳይሆን ዝምታችንም የሚገባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

                                              ሰላም!


ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡ አሁን በሸገር ኤፍ.ኤም ሬዲዮ በጋዜጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሃሳብና አስተያየት ካለዎት በኢሜላቸው honeysolomon123@yahoo.com በፌስቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/honey.solomon.3 ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡

Wednesday, July 10, 2013

"ቦሌ እና ጉለሌ ወይም ሌላ…"

እህሳ እንዴት ሰነባብታችዋል?
የሰሞኑ ወሬ ሁሉ
ፖለቲካ ….ፖለቲካ…
ሹመት…ሹመት….
ሽረት….ሽረት….
ከንቲባ…ከንቲባ ምናምን ሆኗል፡፡ የሹም ሽሩን ነገር "ጉልቻ ቢለዋወጥ…" ነው፡፡ የቤት ምዝገባው ነገር አሁን ላይ ጋብ ያለ ይመስላል፡፡ ደግሞ ነሀሴ ገብቶ እነ 40/60 ሽር ጉድ እስኪሉብን፡፡
"መጀመሪያ የመቀመጫዬን አለች ዝንጀሮ" አሉ? እኔ አሁንም ቀልቤ ከቤቱ ላይ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ቤት ከግድግዳ እና ጣሪያም በላይ ነው፡፡ መቼም የኮንዶሚኒየም ቤት እጣ ተጀመረ ብሎ 80ውን ለመቅደድ ህሊናው የሚፈቅድለት ሰው ሲታይ እንዲህ ብሎ መናገር ያስደፍራል፡፡
ቤት የማይነጥፍ ላም ነውና ሁሉም ሊኖረው ቢኖረውም ለመጨመር ለመጨማመር ያስባል፡፡ ምክንያቱም ቤት ነው፡፡ ከተማዋ ደግሞ አዲስ አበባ…
በርግጥ የችግሩ ስፋት ምንም ያስኮናል፡፡
ቆየት ቢልም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ 5 ዓመት በፊት የተሰራን ጥናት ብነግራችሁ ጨዋታዬን ያሳምረዋል፡፡ በቤት ቁጥሩ ላይ መሻሻል ይኖራል ብለን ብናስብ እንኳ ሰውም የዚያኑ ያህል ተሰግስጓልና ችግሩ  ቢብስ እንጂ ያገግማል የሚል ሃሳብ መስጠት ይከብዳል፡፡
በአዲስ አበባ ከሚገኙ ቤቶች 84.4 በመቶ ያህሉ መኖሪያ ናቸው ቢሆንም ከቤት ፍላጎቱ አንጻር ይህ ቁጥር 60 በመቶ ገደማ እንኳ አይሸፍንም፡፡ በከተማዋ ካሉት መኖሪያ ቤቶች መጪውን 20 ዓመት ሊሸጋገሩ የሚችሉት ደግሞ 35 በመቶው ብቻ ናቸው፡፡
እነዚህ ቤቶች ቤት መባላቸው ብቻ ለኑሮ የተመቹ የሚለውን የሚወክል አይደለም፡፡ የማእከላዊ ስታትስቲክስ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በከተማዋ ከሚገኙ መኖሪያ ቤቶች 75 በመቶው መፀዳጃ ቤት እና 26 በመቶው ማድ ቤት የሌላቸው ናቸው፡፡ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ባለ አንድ ክፍል  ናቸው፡፡
ታሪክን የኋሊት
ቀድሞ አዲስ አበባ ስትቆረቆር የደጃዝማች ፤ የራስ እገሌ ሰፈር እየተባለ የጦር አለቆቹ በስራቸው ያሉትን እያስተዳደሩ ትኖር ነበር ይላሉ የታሪክ ሰዎች፡፡
ከዛማ ጣሊያን ገባ ፒያሳ እና ካዛንቺስ የመደብ ልዩነትን አመጡ፡፡ የሮም ሰዎች ካዛንችስን ለመኖሪያቸው ፒያሳን መገበያያቸው ሲያደርጉ መርካቶ…'ተራ' ተብለው ለተጠሩት አባት አያቶቻችን ለመገበያያነት  ተዘጋጀች፡፡
ጣሊያን ጥፋቷ ሳይበዛ ቶሎ ለቃ መውጣቷ እንዲሁም በቅኝ ግዛት አለመውደቃችን የነጭ የጥቁር ወይም በሃይማኖት ልዩነት የተከፋፈለ አኗኗር እንደሌላው የአፍሪቃ ሀገር ጎልቶ እንዳይወጣ ቢያደርግም በከተማችን እንዲህ አይነቱ የኑሮ መደብን መሰረት ያደረገ አከታተም ብቅ ካለ ሰነባብቷል፡፡
አሁን በአዲስ አበባ የሀብታምና የደሀ ሰፈር አለ፡፡ የተራራቀ የሀብት ልዩነትም እንዲሁ፡፡ በአዲስ አበባ ድሃው ህዝብ በቪዛ እንደሚሄድባቸው ሃገሮች ሩቅ የሚመስሉት ቢሄድም ባይተዋረኝነት እንዲሰማው የሚያደርጉ ሰፈሮች ፤ ሀብታሙ ደግሞ ቀልድ አዋቂ ነን የሚሉ ሙያተኞች ሲቀልድባቸው ከመስማት ውጭ በውል የት እንዳሉ እንኳ በርግጠኝነት የማያውቃቸው ሰፈሮች ተበራክተዋል፡፡
በሪል ስቴት መንደሮች የቤቱ ቀጥተኛ ነዋሪ ካልሆኑ ወይም ቀድሞ እኔጋ እሚመጣ እንግዳ አለ ብሎ ስምዎን ከዘቦቹ የሚያስመዘግብ ሰው ከሌለ በቀር እንዲሁ ዘው የማይባልባቸው በጥርብ ድንጋይ የታጠሩ አደገኛ በሚል የኤሌትሪክ ሽቦ የተከለሉ ግቢዎች ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ አከባቢ መኖር ብቻ አይደለም እምጠይቀው ዘመድ አለኝ ማለት የኑሮ ደረጃዎን ከፍ ያደርጋል፡፡
ቀድሞ ሪል ስቴት እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወይም የኮንደሚኒየም ቤቶች ጉዳይ ነበር ለችግሩ መባባስ እንደምክንያት የሚነሳው፡፡
አሁን ደግሞ 10/90 ፤ 20/80፤ 40/60፤ ……… ተጀምሯል፡፡ ይህ አዲስ የቤቶች ፕሮግራም ቀድሞ የታሰበ እና ዝግጅት ያልተደረገበት መሆኑን የሚያሳብቁ ችግሮችን ገና ካሁኑ ማግተልተል ጀምሯል፡፡ መሰንበት ደጉ ገና ደግሞ ያሳየናል፡፡
የከፍተኛ ሀብታም ሰፈር፣ የመካከለኛ ሀብታም ሰፈር፣ መካከለኛ፣ የድሃ እና የፍጹም ድሃ ሰፈር ብሎ መከፋፈሉ ከዚህ ሰፈር ነኝ ማለት የሚያፍሩ ልጆች እዚህ ሰፈር ዘመድ አለኝ ብለው የሚጠይቃቸው ስጋ የሌላቸው ነዋሪዎችን እንዳይወልድልን ነዋሪውን የማሰባጠሩ ጉዳይ ላይ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባ ነበር… ግን አልሆነም፡፡ እስካሁን ሲነገር የሰማነው የቦታ አደላደል ከፋፍለህ አሳድር አይነት ነው፡፡
10/90 የቤት ፕሮግራም በፍፁም ድህነት ስር ላሉ ዜጎች የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ ፕሮግራሙ መታሰቡ ጎሽ የሚያስብል ነው፡፡ ግን ደግሞ ቤቱ የት ይገነባል? እነዚህን ሰዎች አንድ ቦታ ላይ አጉሮ ማኖርስ አዲስ አበባ ከሌሎች አቻ ከተሞቿ ትሻላለች ያስባላትን የስብጥር ኑሮ አያጠፋው ይሆን የሚለውን ጥያቄ ያመጣል፡፡
አሁን ላይ ምዝገባው በተጠናቀቀው 10/90 የተመዘገበው ሰው ቁጥር ከታሰበውም ቀድሞ ከተጀመሩት የቤቶች ግንባታም ያነሰ ነው፡፡ 187 ብር በወር ቆጥቤ መንግስቴ ለምንዱባን ብሎ እሚሰራው ቤት ከምኖር 274 ብር ቆጥቦ በ20/80 የአንድ መኝታ ቤት ባለቤት ለመሆን ከ900 ሺህ ሰው ውስጥ የተአምር እድል መጠበቅ እመርጣለሁ የሚል ይበዛል፡፡ አሊያም የሰዉ የኑሮ አቋም መንግስት አያውቀውም ማለት ያስችል ይሆና፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በጥናት አልመጣም ያስብላል፡፡
ባለመካከለኛ ገቢው ባለ 20/80ው አንድ ላይ… ውጪ ቀመስ የሆነውን ዲያስፖራ እና ሀገር በቀሉን ባለ ገንዘብ አንድ መንደር ማጎሩ መዘዝ አለው ይላሉ የህብረተሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች፡፡ አብሮ ካለመኖር ካለመተዋወቅ አለመተዛዘን አለመተሳሰብ በጠላትነት መተያየትን ያመጣል፡፡
ኢትዮጵያዊ ሲኖር የሌለው ባለው ይፅናናል፡፡ ሃብታሙም የተቸገረ መኖሩን ሲያውቅ ነው ተመስገን የሚለው፡፡
ድሃው ድርሽ የማይልባቸው ቢመጣ እንኳ ቀኑን ሙሉ ለባለጠጋው ጉልበቱን ሲሸጥ ውሎ የሚመለስባቸው ሰፈሮች በአንድ አንድ ሀገሮች አሉ ይባላል በአፍሪቃ፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪቃም ነች ስንል ከደሃው እየነፈግናት አይደለም፡፡ አንተ የእንትን ሰፈር ልጅ ተብሎ የሚሰደብ፣ እኔ የዚህ ሰፈር ልጅ ነኝ እያለ ሌላው ቆዳውን የሚያዋድድባት ከተማ ልትሆን አይገባም፡፡
ቢታሰብበት አይበጅም?

ቸር ሰንብቱ!


ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡ አሁን በሸገር ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኛ ናቸው፡፡ ሃሳብና አስተያየት ካለዎት በኢሜይላቸው honeysolomon123@yahoo.com በፌስቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/honey.solomon.3?fref=ts ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡

Wednesday, July 3, 2013

የቦሌው መንገድ - ላለው ይጨመርለታል

        ልማትን አጥብቆ የሚወደው ኢ-ቲቪያችን የቦሌን መንገድ አስመልክቶ አንድ የቢዝነስ ወሬ አቀረበ፡፡ ከመስቀል አደባባይ አውሮፕላን ማረፊያ (ቻይና አደባባይ መሠለኝ) ያለው መንገድ ስራ አልቆ ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ውሏል አለ፡፡ እናም በመንገዱ ስራ ምክንያት ስራቸው ቀዝቅዞባቸው የነበሩት የንግድ ቤቶች አሁን ገበያው ድርላቶቸዋል ብሎም ጨመረ፡፡ አንዳንድ ገበያችን ከ 70 በመቶ ወደ 85 በመቶ ጨምሯል የሚሉ ጥናት ሳይሰሩ በመቶኛ መነጋገር የሚቀናቸውን ነጋዴዎችም አስተያየታቸውን ሰጡ ፡፡ አይ ጥሩ ነው እንኳንም ገበያችሁ ደራ ብለናችኋል፡፡ እነዛ የመንገዱ ስራ በተባለው ጊዜ ባያልቅ ቤተሰቤን ምን እመግባለሁ ብለው የሰጉ ነጋዴዎች ግን ንግዳቸውን ወደ ሌላ ሰፈር ቸኩለው አዛወሩ፡፡ ይሄው ዛሬ ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ እንደሚባለው ሌላ ሰፈር መተዳደሪያ ሱቅ  የነበራቸው እና አንዳንድ ተስፋ በቀላሉ የማይቆርጡ ነጋዴዎች  ጥርሳቸውን ነክሰው ሰንብተው በዛሬው የደራ ገበያ ፈገግ ፈገግ ለማለት በቁ፡፡ ከዚህ ወጣ ያሉት የቦሌን መንገድ በእግርና በታክሲ የሚያቋርጡት መኪና የሌላቸው ዜጎች ግን ‹ስራው ተጠናቀቀ› የተባለው የቦሌ መንገድ ‹መቼ ተጠናቀቀና?› እያሉ ነው፡፡
ሚዲያዎች ማንን መሠረት አድርገው እንደሆነ እንጃ መንገዱ ተጠናቋል ብለው ይዘግቡ ከጀመሩ ሰነበቱ፡፡ ባለስልጣናትም ከሳምንታት በፊት በመንገዱ አካፋይ ላይ ለምለም ቅጠል ሻጥ ሻጥ ተደርጎላቸው ስራችንን ጨረስን መኪናም አስተላለፍን ብለው መጥተው መረቁት፡፡ እርግጥ ቅጠሎቹ አሁን ደርቀዋል፡፡ የአስፋልት ጥቁረት ምን መምሰል እንዳለበት የሚከራከሩ ባለመኪኖች ደግሞ ‹መንገዱ አላለቀም፡፡ ምክንያቱም ይሄ ጭቃ መሰሉ ነገር ጠፍቶ ድብን ያለ ጥቁር መሆን ስለሚገባው ገና አንድ ዙር አስፋልት ማልበስ እና ማስዋብ ይቀረዋል፡፡› እያሉ ነው፡፡ እነዚህ ባለመኪና የመንገዱ ተጠቃሚዎች በፊት በፊት ‹የቦሌ መንገድ የትራፊክ መጨናነቁ ገደለን መንገዱ ሰፋ ቢል ጥሩ ነበር፡፡› በሚል አብዝተው ሲማረሩ የኖሩና አሁን ፀሎታቸው ተሰምቶ የመንገዱ ስፋት የሚሆኑበት ጨንቋቸው በከፍተኛ ፍጥነት እየበረሩበት ያሉ ናቸው፡፡ ዛሬ ጠዋት አንዲት እናት ዕድሜአቸው በማይፈቅደው ሩጫ ነፍሴ አውጪኝ ብለው አስፋልት ከተሻገሩ በኋላ ቁና ቁና እየተነፈሱ እንዲህ አሉ ‹አሁንማ መንገዱም ሰፋላቸው!›፡፡ ባለመኪኖቹ በመንገድ ግንባታው ወቅት መንገድ ቀይረው፣ በመንገዱ መጣበብና መጨናነቅ ለረዥም ደቂቃዎች መኪናቸው ውስጥ ተቀምጠው ያሳልፉ የነበረበት ጊዜ ላይ ለመሳለቅ ይመስላል አሁን በአጭር ደቂቃ የፈለጉት ቦታ የመድረሳቸውን ተዓምር እያደናነቁ እንደጉድ ይበራሉ፡፡ እያደናነቁም ግን ‹መንገዱማ የማስዋብ ስራ›ይቀረዋል ይላሉ፡፡
የቦሌን መንገድ በስራም ሆነ በመተላለፍ አጋጣሚ የሚያዘወትራት እግረኛ በተመሳሳይ/በሚያስገርም ተቃርኖ ‹የቦሌ መንገድ አላለቀም!› ብሎ በድፍረት እየተናገረ ነው፡፡ ምክንያቱም የእግረኛ መረማመጃው ገና ኮረት እንደተከመረበት ነው፡፡ ጉድጓድም ሞልቶታል፡፡ እግረኞች የእግረኛ መንገዱ ገና በስራ እና በቁፋሮ ላይ በመሆኑ ከፈጣን መኪኖች ጋር ትከሻ ለትከሻ እየተጋፉ በመኪና መንገድ ላይ እየተጓዙ ነው፡፡ መሻገሪያ መራመጃ አጥቶ ሁለት ዓመት የተንገላታው እግረኛው ነው፡፡ ታክሲ የሚሳፈርበት እና የሚወርድበት ቦታ አልመች ብሎት ለልማቱ ሲባል ‹ቻለው› የተባለው እግረኛው ነው፡፡ አቧራ እና ጭቃ ተፈራርቆበት ለዓይንና ለባክቴሪያ ህመም እና የህክምና ወጪ የተዳረገው እግረኛው ነው፡፡ 3 ብር ከ70 ይከፍልበት ለነበረው መንገድ 8 ብር እየከፈለ የሄደው እግረኛው ነው፡፡ ለእግረኛው መንገዱ የሚጠናቀቀው ስቃዩ ሲጠናቀቅ ነው፡፡
አዲሱ የቦሌ መንገድ አምሮበታል፡፡ መኪና የሌለው ደሀ (እግረኛ)  አልይ ያለ ይመስላል፡፡ በየመሀሉ ለእግረኛ የሚሆን መቋረጫ እንዲኖር አልፈቀደም፡፡ ታክሲዎችም እዛም እዛም እየቆሙ እንዲጭኑና እንዲያራግፉ አይወድም፡፡ ስለዚህ እግረኛ ስሙም ከነመጠሪያ እግረኛ ነውና በእግሩ እንዲሄድ ተፈርዶበታል፡፡ ለምሳሌ ከፒያሳ ደንበል ህንፃ ድረስ በታክሲ መምጣት የሚፈልግ ሰው ቀደም አድርጎ ፍላሚንጎ ጋር ወርዶ በእግሩ እንዲሄድ ይጠየቃል፡፡ ባለታክሲዎቹ መንገዱ በሙሉ ‹ክልክል በክልክል› ሆነብን ብለው ያማርራሉ፡፡ ማውረድ ክልክል ነው፡፡ ተሳፋሪውም ታሪፉ እንኳን ቢቀነስልን ብለው ያሳቅላሉ፡፡ አንድ ወቅት ላይ የህዝብ ማመላለሻ ዋጋ ታሪፍ በመንግስት አባባል ‹ሲሻሻል› በህዝቡ አቀባበል ደግሞ ‹ሲጨምር› ይመለከተኛል ያለው የመንግስት አካል ህዝቡ በኪሎሜትር መክፈል ያለበትን ዋጋ በጋዜጣ አትሞት ነበር፡፡ ለአብነት ያህል በጋዜጣው ስሌት መሠረት ከፒያሳ ደንበል ሸዋ ዳቦ የሚወስደው የታክሲ ዋጋ 2 ብር ከ70 ሳንቲም ነው ብሎ አወጀ፡፡ ጋዜጣውን እማኝ አድርገው መክፈል ያለብን 2፤70 እንጂ 3፡70 አይደለም ብለው የተከራከሩ ተሳፋሪዎች ከታክሲ ሾፌሮች ግልምጫ ከረዳቶቸ ደግሞ እርግጫ (ቀረሽ) ምላሽ ሲደርስባቸው ብሶታቸውን ለሚመለከተው አምላክ ሰጥተውት ዝም አሉ፡፡ የቦሌው አዲሱ መንገድ ደሀውን ከሳንቲሙም፣ከጉልበቱም ከጊዜውም፣ በጥቅሉም ከልማቱም ያስተረፈለት የለም፡፡ ታዲያ መንገዱ ለደሀው እግረኛ ምኑ ነው? ለባለመኪና ፍጥነት ጨምሯል ለእግረኛው ስቃይ ጨምሯል፡፡ እንግልትም ምቾትም እንዴት ላለው ይጨመርለታል?


አንዳንድ ሀገራት ለህዝባቸውም ርካሽ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፓርት ማቅረብ ሲታክታቸው ሰፋፊ መንገዶችን ይሠሩና ህዝባቸው መኪና እንዲገዛ ያበረታታሉ፡፡ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ መንገዶች ለእግረኞች ሳይሆን ለባለመኪኖች እንዲመቹ ተደርገው እየሰፉ ነው፡፡ እግረኛው በእግሩ እና በታክሲ መሄድ አላዋጣው እንዲለውና የራሱን መኪና እንዲገዛ ከሆነ እሰየው፡፡ ሆኖም መኪና የገዙ ፣ለመግዛት ያሰቡ በአጠቃላይ የመግዛት አቅሙ ያላቸው ሰዎች መኪና ቀረጥ መቶ ሀምሳ እጥፍ መሆኑ የሚቀመስ አላደረገው እያሉ እያማረሩ ነው፡፡በዛ ላይ ገንዘቡስ ከየት ይመጣል? በሌላ በኩል ጠባብ መንገድና ከተማ እንዲሁም በርካታ ህዝብ ያላቸው ሀገሮች የመኪና ዋጋን ሳይሆን የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በማሳጣትና ኪራዩንም በማስወደድ መኪና ለምኔ ብሎ እንዲተውና በተለይም በከተማ ባቡር እንዲጠቀም ያደርጉታል፡፡ አዲስ አበባ የከተማ የባቡር መንገድ እየተዘረጋ መሆኑ ህዝቡ መኪናም ባይኖረው የትራንስፓርት ፍላጎቱ እንዲሟላለት ይመስላል፡፡  የሚመስለንን ትተን እውነቱን እንጠይቅ፡፡ መንግስት ህዝቡ መኪና እንዲኖረው ፈልጓል ወይስ አልፈለገም? መንገድን ለማን ነው የሚሰራው? ለሞላው ለተደላደለው? ወይስ ላጣው ለነጣው? የቦሌው አዲሱ መንገድ በሁሉም የኢኮኖሚ ደረጃ ያሉትን ዜጎች እኩል ለማገልገል ታስቦ እንዳልተሰራ እያሳበቀ ነው፡፡ ለደሀው ተብሎ የለማው መንገድ የቱ ነው? ልማት ማለትስ ምን ማለት ነው?


ጸሃፌ ተውኔት መዓዛ ወርቁን በሸገር የአልጋ በአልጋ ተከታታይ ድራማና በህይወት መሰናዶ ድራማ ደራሲነታቸው እናስታውሳቸዋለን፡፡ አሁን እየታየ የሚገኝ ዝነኞቹ የተሰኘ ቴአትርም አላቸው፡፡ አስተያየት ካላችሁ በፌስቡክ አድራሻቸው በኩል በhttps://www.facebook.com/meaza.worku.39 ሊያገኙዋቸው ይችላሉ፡፡

Wednesday, June 19, 2013

ትዝብት በእንዳለ : እናት ለምን ትሙት ትሂድ አጎንብሳ,,,


 አዲስ አበባ ግንቦት 28፣2005 ዓ ም  :: መንግስት ባወጣው የ 10/ በ90፣20/በ80፣40/በ60 አዲስ ቤት መስሪያ የቁጠባ ደብተር ለማውጣት ከክፍለ ሀገር በመጣው ቀን በበነጋው  ዕለተ ዕሮብ ግንቦት 28፣2005 ነበር:: ቃሊቲ ሚድ ሮክ አከባቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ  እኔም እንደዜጋና እንደ አንድ አዲስ አበባ ነዋሪ ቤት መስሪያ የሚሆነኝን ቁጠባ ደብተር ለማውጣት ታላቅ ወንድሜ ከለሊቱ 9:00 ሰዓት ከቤት ወጥቶና 45ኛ ሆኖ በተመዘገበልኝ ተራ ጠብቄ ለመመዝገብ ነበር እዚያ የሄድኩት::  
ታዲያ ባንኩ ከዋናው መንገድ ማለትም ከቃሊቲ ወደ ደብረ ዘይት ከሚወስደው አውራ ጎዳና በስተ ቀኝ ዳር ላይ የሚገኝ ሲሆን :: ከተመዝጋቢው ህዝብ ብዛት የተነሳ ሊመዘገብ ሰልፍ ከያዘ ሰው በተጨማሪ ሰልፍ ሳይዝ የቆመው ሰው አስፋልቱ ጠርዝ ድረስ በቡድን በቡድን እየሆኑ በቤቱ ምዝገባ ላይ የየራሱን ወግ ይዟል ::
አንዱ ቡድን ስለ ህገ ደንቡ እንዲያስረዳ አንዱ የቡድን አባል በጠየቀው ጥያቄ ሁሉም እኔ የገባኝ እንዲህ ነው በሚመስሉ መልኩ ለማስረዳት በመንግስት በተዘጋጀው በራሪ ወረቀት ላይ አንገታቸውን ደፍተዋል:: ከሌላኛው በቡድን ሆነው ከቆሙት መሀከል ደግሞ በዚህ ጉዳይ ብቻ ከስራ ላይ የመጣ የሆነና እዚህ ሶስት ቀናቶችን እንዳሳለፈና ነገር ግን አሁን ወደ ሥራም ለመመለስ እያመነታ መሆኑና ከሁለት ያጣ እንዳይሆን ስጋቱን ለቡድኑ አባላት ያጫውታቻዋል::
 እኔ ለብቻዬ ተነጥዬ ቆሜ ስለነበር በደብ በህዝቡ መሀል ያለውን ነገር መታዘብም ሆነ መመልከት እችል ነበር:: ቢገርማችሁም ባይገርማችሁም ከግማሽ በላይ ህዝብ ጋቢ፣ ሹራብና ካቦርት የለበሰ ነበር ታዲያ ይህ ምን ሊገርመኝ ወንድሜ እኮ 9: 00 ሰዓት ከለሊቱ ወጥቶ እኮ ነው 45ኛ ሆኖ የተመዘገበልኝ :: ይህ ህዝብ ደግሞ ወይ ስምንት ሰዓት ወይ ደግሞ ከዚያ በፊት ሊሆን ይችላል ከቤቱ የወጣው ::  ቤት ፍለጋ ከቤት ውጭ ማደር !
ይህን ትዝብቴን  እንድጭር ያስገደደኝን ዋና ጉዳይ  የሆነውን ዋና እርእሴን አልዘነጋውም። ይሄውላቹ ,,,ወጭ ወራጅ መኪና በዚያ ሲያልፍ ክላክስ ጥሩንባ ያሰማ ነበር :: ምክኒያቱም ጽሁፌን ስጀምር ጠቅሼላቹ ነበር የባንክ ቤቱና አስፋልቱን እርቀት በግምት 16 ሜትር ያህል ነው:: ታዲያ ስም ዝርዝራችንን ሲመዘግቡ መታወቂያችንን ሰብስበው ስለነበር ዕሮብ የተመዘገብነውን ሁሉ ለዓርብ እንድንመለስ ከነገሩን በኋላ መታወቂያችንን ለሶስት ግለሰቦች እንዲመልሱልን ሰጡዋቸው::
የእኔና የሌሎችን መታወቂያ የያዘው ግለ ሰብ መታወቂያችንን ሊመልስልን የሰበሰበን ከአስፋልቱ ጠርዝ ላይ ስለነበር ሰዎች ሲከቡት ሰዉ ከአስፋልቱ ላይ ወጥቶ ነበር:: ኤኬሌ,,, ኤኬሌ,,, ኤኬሌ,,,እያለና ግለሰቡ አቤት ሲል ሰጪው መልኩን ከመታወቂያ ላይ ካለ ፎቶ ጋር እያመሳሰለ ይመልስ ተያይዟል :: ታዲያ አንድ የከባድ መኪና (ሳኒዮ) የጥሩንባ ድምጽ የተሰበሰበውን ህዝብ አስደነበረው :: የመኪናው ጥሩንባ ድምጽ ከፍተኛ ስለነበር ሁሉም ሰው የስድብና የእርግማን ዓይነት ውርጅብኝ ያወርድበት ገባ::   ታዲያ ከዚያ ሁሉ ስድብ፣እርግማንና ከመኪናው ጥሩንባው ጩኧት ይልቅ ጆሮዬ የገባው ድምጽ አንድ አጠገቤ መታወቂያ ሊወስድ የቆመ ወጣት ድምጽ ነበር። አስቀያሚ ስድብ ,,,መቼም የስድብ ጥሩ ባይኖረውም ሹፌሩን አቦ እናትህ እንዲ ላድርግ ብሎ ሲሳደብ ነበር:: እኔ የምገባበት ጠፍቶኝ እንደመሸማቀቅ ብዬ አንገቴን ትከሻዬ ውስጥ ቀብሬ ቀና ስል አንድ እንደ እኔው ስድቡ ልቧን የሰበረባት መልከ መልከም ሴት ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጨን :: ይህ ወጣት መጀመሪያ ዓመት የዩንቨርሲቲ የዶርም አባል የሆነውን ልጅ ትዝ እንዲለኝ አስደረገኝ :: ይህ የዶርም አባል የነበረው ልጅ አንድ ቀን FRESH MAN ገና እንደገባን እንዲህ ብሎ ስለሰደበኝ ብቻ ከግቢው በውጤቱ ማነስ (AD) ሆኖ እስከባረር ድረስ አንነጋገርም ነበር::
አቦ በእናታችሁ  ስለእናታችሁ ብላችሁ  እናት የብዙ ነገራችን ምሳሌ ነች እኮ
እ    እ  እ   እ    እ   ናት!
የ ጭንቋ የምጧ የእመሟ ድምጽ ናት::
አዲስ አበባ

ግንቦት 28፣2005 

Wednesday, June 12, 2013

የተጣጣፉት ሜኑዎች


አንዱን ቀን ከሁለት የቅርብ ወዳጆቼ ጋር ምግብ ቢጤ ፈላለግንና ወደ አንዱ ሆቴል ገባን፡፡

የምርጫችን ምክንያት “ትላንት የበላነው ቆንጆ ምግብ አለ...ዋጋውም መልካም ነው” የሚለው የገበታ ሸሪኮቼ ምክንያት ነው፡፡

ከመግባታችን ትላንት በላን...በ70 ብር ይሸጣል ያሉትን ምግብ አዘዝን፡፡

አስተናጋጁ ጠረጴዛውን አፀዳድቶ ሜኑ ይዞ ከተፍ አለ፡፡

“ፍሬንድ ነገርንህ እኮ” አለው አንዱ ከመካከላችን ፤ አስተናጋጁ ደግሞ “ወዳጄ የዋጋ ጭማሪ ስለተደረገ ትስማሙ እና አትስማሙ እንደው ብታዩት ይሻላል ብዬ ነው” አስረዳ፡፡

ሜኑው ተገለጠ፡፡ እንዳለቀ ሱሪ የተጣጣፈ ይበዛዋል፡፡

ትላንት 70 ብር ተበላች የተባለችው ምግብም ለመልስ እንዳታስቸግር ድፍን 100 ሆናለች፡፡

ጠላታችሁ ክው ይበል!

እኔም እንዲሁ ነው ድንግጥ ያልኩት፡፡ በአንድ ቀን አዳር? ጬሂ ጬሂ ያስብላል፡፡
ግን በየት በኩል? ማንን ደስ ይበለው ብዬ? ዋጥ ማድረግ እየተቻለ፡፡

“ለምን?” አልነው አስተናጋጁን፡፡

አስተናጋጁ የሚገባበት ጠፍቶት “ምንም አላውቅም፡፡ ትላንት ከሰአቱን እረፍት ነበርኩ ዛሬ ስመጣ ዋጋ ማስተካከያ እንደተደረገ ሰማሁ” አለ ቁልጭ ቁልጭ እያለ፡፡
የፈጣሪ ያለህ! ለማን አቤት ይባላል?

ያን ቤት በንዴት ብቻ ለቀን ወጣን፡፡ እኔ በበኩሌ በዛው ቀረሁ፡፡

ወዳጆቼ አሁን አሁን በአዲስ አበባ ካፌዎችና ምግብ ቤቶች ቋሚ የሚባል ነገር ጠፍቷል፡፡
ትላንት ያገኛችሁትን አገልግሎትና ዋጋ ዛሬ እንደሚያገኙ ርግጠኛ መሆን ለብዙ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ከብዷል፡፡

ሜኑዎቻቸው እንደ አየር ጠባዩ አሁንም አሁንም ይቀያየራል፡፡

ከምግብ ዝርዝሮች ፊት ለፊት ያሉት የዋጋ ተመኖች በቁርጥራጭ ወረቀቶች ተለጣጥፈው የቀድሞ ይዞታቸውን ለቀዋል፡፡

የንግድ ቤቶቹ ባለቤቶች ዋጋ ለመጨመር የሚወስድባቸው ፍጥነት በላስቲክ የለበጡትን ሜኔዎች በወጉ ለመቀየር እንኳ ጊዜ የሚሠጥ አይደለም፡፡

ታሸገው ከሚሸጡት ውሃና ለስላሳ ጀምሮ ምግብ ፣ ካፌ አፈራሽ መጠጡ ፣ሻይን ጨምሮ ሃገር አማን አይደለም እንዴ በሚያስብል ፍጥነት ያሻቅባሉ፡፡

ጭማሪው ደግሞ እስቲ ይሁና ለማለት እንኳ ትዕግስት አይሠጥም፡፡ ሊያውም መጠኑ እንዳለ ካለ፡፡

አንዳንዴ ትላንት ወይም በዚህ ሳምንት የበላሁት ነው፣አንዱ ሁለት ሰው አጥግቦ ይመልሳል ያሉትን ምግብ ወዳጆን ሊጋብዙ ሲሄዱ ከርሶ አንጀት እንኳ ጠብ የማትል ኪኒን የምታክል የምትሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ያሸማቅቃል!

እንዲህ ያለውን ድንገቴ የዋጋ ጭማሪ በካፌው ላይ አነሳን እንጂ በብዙ ምርትና አገልግሎት ላይ የሚታይ ነው፡፡
መቼም እንደ ዜጋ ሁሉኑም ማስደንገጡ ባይቀርም ጭንቁ የሚበዛው የወር ገቢው ተቆጥሮ ለምትሠጠውና እዚህጋ ዋጋ ጨምሬ ላካክስ በማይለው ቅጥር ሰራተኛ ላይ ነው፡፡

የቤት ኪራዩ ሲንር ወርሃዊ የትምህርት ቤት ክፍያው ሲጨምር ዶላር እዚህ ገባ እየተባለ ብጣሸ ጨርቅ ለመልበስ የወር ደሞዝን ሲገዳደር ታክሲም መንገድ ግንባታው አንድ መታጠፊያ ጨመረብኝ ብሎ ሳንቲም ለመመንተፍ ሲሯሯጥ  መቆጣጠር የሚገባው ቢሮ ተቀምጦ “ህገ ወጥ ነው፡፡ ያስቀጣል” ከማለት ባለፈ ህግን መጣስ እንደሚያስቀጣ ሳያሳይ ሲቀር ተጐጂው ይህው ግብሩን ያለ አንዳች ሽርፍራፊ የሚከፍለው ደሞዝተኛ ነው፡፡

ቀነስ ብሎ የሚገዛው ነገር ያጣ ሠው፣ ግሸበቱ ቀነሰ ወደ አንድ አሀዝ ወረደ 6 በመቶ ገባ ገለመሌ ቢባል ቁጥር እንጂ ምን ትርጉም ሊሠጠው ይችላል?

ምክንያቱ ላይ ደግሞ እናውራ

እኔ እኛ ተጠቃሚዎቹን ከመውቀስ እጀምራለሁ፡፡

ዘመናችን እራሱ የተወደደ ነገር ሁሉ ትክክልና የሚሻል የመሰለበት ነው፡፡
የልባችንን የሚያውቁት ነጋዴዎቹም ዋጋውን ሰማይ ሰቅለው የእቃውን ጥራት በዋጋው ውድነት እንድንለካው በማዘን ያስቀምጡልናል፡፡

አንድ ከፈረንሳይ የመጣ ወዳጄ የካፌ ቢዝነስ ያበላል ተብሎ የከፈተውን ሬስቶራንት ልመረቅ ገና በ4ኛ ቀኑ ሄጄ የሱም ሜኑዎች ተለጣጥፈው ሳይ ተገርምኩ፡፡ “አንተም?” ብለው፡፡
“ምን ላድርግ ብለሽ ነው ቀድሞ ብሎ የወጣውን ዋጋ ያዩ ጓደኞቼ ቤትህን ርካሽና መናኛ ያስመስለዋል በል ቆልለው በለውኝ ነው” ብሎኛል፡፡

ቀድሞ የነበረውን ወጪ እና ገቢውን አሰልቶ ያተርፈኛል ብሎ የወሠነውን ሒሳብም መቀየር ያስፈለገው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡  
በርግጥ አንድ ሰው የካፌና የምግብ ቤት አገልግሎት ልሰጥ ብሎ ስራ ሲጀምር የራሱ የሆነ ብዙ ወጪ አለው፡፡ የቤት ኪራይ ይከፍላል ሰራተኛ ይቀጥራል የጥሬ እቃ ወጪ ይጠብቀዋል፡፡ የመብራትና ውሃም ይቆርጣል… ሌላም ሌላም፤

ከነዚህ አገልግሎቶች የሚቀበለው ገንዘብ ግን በትክክል ለሚሠጠው አገልግሎት እና ለሚያገኘው ተገቢ ትርፍ ብቻ ነው ወይ? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡

መሸቶ በነጋ ቁጥር ለሚጨምረው ዋጋ መሸቶ ሲነጋ የቤት ኪራይ እየጨመረ? የመብራትና የውሃ ዋጋ እየናረ? ለሠራተኞቹ ደሞዝና ጉርሻ እንዲሁም ጥቅማጥቅም እየሠጠ? ወይስ ሌላ?

አንድ ኪሎ ቲማቲም በ5 ብር ሲጨምር በአንድ ምግብ 15 ብር ሚቆነድደን ነጋዴ  ሲቀንስስ ይቀንሳል እንዴ?

ለተጣጣፉት የአዲስ አበባ ሜኑዎች ምን ምክንያት አንስቶ ማሳመን ይችላል?


                       ቸር ያሰማን!



ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡ አሁን በሸገር ኤፍ.ኤም ሬዲዮ በጋዜጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሃሳብና አስተያየት ካለዎት በኢሜላቸው honeysolomon123@yahoo.com በፌስቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/honey.solomon.3 ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡

Wednesday, June 5, 2013

ስሜን ያየ!

ዝም ብሎ መተራመስ ምንድነው?
የአዲስ አበባን ውሎ ማወቅ የፈለገ በስራ ቀን ቢሮ መግባቱን ትቶ አንዱ ኢንተርኔት ካፌ ጎራ ይበል፡፡ ለካ ስንት ነገር አምልጦኛልና የሚል ቁጭት ይፈጠርበታል፡፡ ትላንት ሰኞ ግንቦት 26 በእረፍት ስም ቢሮ ሳልገባ ብውል ሀገሪቱን እና ህዝቦቿን ስታዘባቸው ዋልኩ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከሳምንታት በፊት ባንክ ሄጄ መታወቂያዬን አዩና ሌላ የሚረባ መታወቂያ ካለሽ አምጪ ይሄኛው ሳይታደስ 2 ዓመት ያለፈበት ነው ተባልኩ፡፡ መቼ ወደ ቀበሌ መሄድ እንዳለብኝ የመከረኝ ደህና ዘመድ ስላልነበረኝ ከዛሬ የተሻለ ቀኝ አላገኝም አልኩና ሰኞ ወደ ከሰዓት በኋላ ከቤት ወጣሁ፡፡ አስቸኳይ  ፎቶ ተነሳሁ፡፡(‹አስቸኳይ ፎቶ አለ?› ተብለው ሲጠየቁ ‹አለ ግን ለዛሬ አይደርስም› የሚሉ ፎቶ ቤቶች አሉ ብለው ካሳቁኝ ሳምንት አልሞላውም፡፡ የኔው ከ35 ደቂቃ በኋላ የሚደርስ ነበር) እስከዛው ኢንተርኔት ካፌ ልቆይ ወሰንኩ፡፡ ቤቴ ለፎቶ ቤቱ ይቀርባል፡፡ ኢንተርኔት ካፌው ደግሞ ለፎቶ ቤቱ ይቀርባል፡፡ ከኢንተርኔት ካፌው በቅርብ ርቀት ላይ ውዱ ቀበሌአችን ይገኛል፡፡
ሳላስበው ለአንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ በኢንተርኔት ካፌው ስቆይ ሰዎች እየመጡ እንዲህ ይጠይቁ ነበር፡፡
‹ስሜን ታዩልኛላችሁ?›
< ፎቶ ኮፒ አለ?›
‹  መመሪያውን ታሳዩኛላችሁ?›
‹ፎቶ ኮፒ›
‹የኮንዶሚኒየም ምዝገባ ካርዴ ይኸው! ስሜ - - -›
ወጣት ሴቶች፣አሮጊቶች ሽማግሌዎች፣ጎልማሳ ወንዶች  - - - ከኢንተርኔት ጋር ትውውቅ የሌላቸው ግራ የገባቸው ዜጎች ኢንተርኔት ካፌዋን በስራ እና በጥያቄ ብዛት ወጥረዋታል፡፡ ሲያቀብጠኝ ብዙ ሊያቆየኝ የሚችል ኮፒ የሚደረግ ጉዳይም ይዤ ነበር የሄድኩት፡፡በየጣልቃው የቤት አዳኞቹን ፎቶ ኮፒ ስለምትሰራ ካሰብኩት ትንሽ አቆይቶኛል፡፡ በቃ ኮፒው እስኪያልቅ ፎቶዬን ይዤ ቀበሌ ደረስ ብዬ ልምጣ አልኩና ሄድኩ፡፡
ቀበሌው በሰው ብዛት ጢም ብሏል፡፡በፊት መታወቂያ  የሚታደሰው አዲስ በተገነባው የቀበሌው ፅህፈት ቤት ህንፃ ላይ ፤በአንድ መስኮት፤ 5 ደቂቃ ላልበለጠ ጊዜ በሚሰጥ አገልግሎት ነበር፡፡ አሁን ከፎቁ ወርደው በአንድ ነባር አሮጌ አዳራሽ ወርደዋል፡፡‹ወደ ህዝቡ ቀረብ እንዲሉ ነው› ብላ ቦታው የተለወጠበትን ግምቷን ያካፈለችኝ ሴት ነበረች፡፡ አዳራሹ ውስጥም ከአዳራሹ ውጪም ሰው እንደጤፍ ፈሷል፡፡
‹ምንድነው ይሄ ሁሉ ሰልፍ?› አልኩ
‹መታወቂያ  ለማሳደስ›
‹እስከዛሬ የት ከርመው ነበር?› አላልኩም፡፡ እኔ ራሴ የት ከርሜ ነበር?
የሰልፍ ቁጥር ደግሞ ይታደላል፡፡ 68 ሰዎች ቀድመውኛል፡፡ 69 ቁጥርን ተቀብዬ በማግስቱ ለመመለስ ቁጥር ወደሚሰጠው ሰው ሄጄ ስጠይቀው፡፡ ‹ቆይ ወረፋ ይዘሽ ጠብቂ የተሰጠው ቁጥር ሲያልቅ ነው አዲስ የምንሰጠው› አለ፡፡ ህዝቡን እንዳሻው ሲያደርገው አሳላፊው ፊት ላይ የነበረው ደስታ ልጁን የሚድር እንጂ መታወቂያ ለመውሰድ የመጣ ሰው የሚያሰልፍ አይመስልም፡፡ የቀበሌው ጊቢ ውስጥ ትዳር አለመያዛቸውን ለማስመስከር በሚሯሯጡ ሰዎችም ተሞልቷል፡፡ ‹እንደዚህ አይነት ሰርግና ምላሽ ውስጥ መቆየቱ አያዋጣኝም› አያልኩ በውስጤ እያልጎመጎምኩ ፤ግርግሩ እስኪበርድ ወደ ቀበሌ ድርሽ እንደማልል ለራሴ ቃል እየገባሁ ወደ ኢንተርኔት ካፌው ተመለስኩ፡፡
የኢንተርኔት ካፌው ባለቤትና የኔን ኮፒ እያደረገች የዛን ሁሉ ሰው ጥያቄ ስታስተናግድ የነበረች ልጅ በወሬ ጠመድኳት፡፡
‹እኔ የምልሽ ምንድነው ትርምሱ?›
‹10 በ90 እና 20 በ80 ቤት ለመመዝገብ የባንክ አካውንት ክፈቱ ተብሏል›
‹ታዲያ ስማችንን እዩልን የሚሉት ለምናቸው ነው?›
‹ ከዚህ በፊት ኮንደሚኒየም የተመዘገቡት ናቸው፡፡ ቢጫ ካርዷን ይዘው ይመጡና ስማችንን እዩልን ይላሉ፡፡ እሱ ዝርዝር ደግሞ እኛ ጋር አይገኝም፡፡›
‹የት ነው የሚገኘው?›
‹እኔጃ! እዛው ቤቶች ልማት ይሆናል፡፤ ኢንተርኔት ላይ መኖሩንም የነገረን የለም›
‹ለምንድነው ስማቸውን የሚፈልጉት?›
‹ይጠፋል አሉ›
‹ወዴት ይጠፋል?›
‹በቃ ይጠፋል፡፡ እልም እልም ብሎ ይጠፋል፡፤የእኔ እህት አሁን ከተመዘገበችበት ስሟ ጠፍቷል፡፡ እንዳትከስ ደግሞ ቢጫ ካርዷን አጣችው›
‹ታዲያ የአዲሱ ምዝገባ ዕለት እዛው ሄደው ጠይቀው ጠፍቶ ካገኙት ከመንግስት ጋር አይነጋገሩም እንዴ?›
‹ እኔ ምን አውቃለሁ ሰው ዝም ብሎ መተራመስ ይወዳል፡፡ አሁን ቅድም የመጣቸውን ሴትዮ አይተሻታል? ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ስሟን ፍለጋ ስራ አቁማ ከቢሮ የወጣች እስካሁን ሳታገኘው ይሄው 9 ሰዓት ሆነባት፡፡ ተይ ስምሽን ኢንተርኔት ካፌ አታገኚውም ብንላት የቤት ዕጣዋን የወሰድንባት ይመስል እንደጠላት አየችን፡፡ ደግሞ ለዛ ውሀ ላይ እየተተከለ ለሚሰምጥ ቤት፡፡ ሁለት ኮንደሚኒየም እኮ ሰምጧል አልሰማሽም?››
‹ከሰማሁ ቆይቻለሁ፡፡ ግን እኔ ዘንበል እንዳለ ነው የቆምኩት መስመጡን አልነገሩኝም፡፡ - - -እኔ የምለው ግን ፤እናንተ ዛሬ ስራ የበዛባችሁ ምን እየሰራችሁ ነው?›
‹የባንኩን ፎርም እና መታወቂያ ፎቶ ኮፒ እናደርጋለን፡፡ መመሪያው ደግሞ ፋና ዌብሳይት ላይ አለ እሱን እናሳያለን፡፡ምን እንደሚያስፈልግ ዌብሳይቱ ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል፡፡ እሱን ቢያዩኮ መቼ መምጣት እንዳለባቸው ስለሚያውቁ ግርግሩም ትንሽ ቀነስ ይል ነበር፡፡ለምሳሌ የ40በ 60 ምዝገባ ገና ነሀሴ ላይ ነው፡፡ ሰው ግን ግርግርና መንሰፍሰፍ ይወዳል፡፡›አለችኝ እንግፍግፍ እያለች፡፡
‹እስኪ ለኔም አሳዩኝ› አልኳት፡፡ አንዱ የኮምፒውተር ስክሪን ፊት አስቀመጠችኝ፡፡ ለነባር(ከዚህ በፊት ኮንደሚኒየም ዕጣ ላይ ለመግባት ለተመዘገቡት) እና  ለአዲሶች ተብሎ ተለይቷል፡፡ አዲስ ተመዝጋቢ ሲኮን በየወሩ የሚቀመጠው ተቀማጭ ከነባሮቹ ይቀንሳል፡፡ ቀደም ብዬ የሰማሁት ቢሆንም የኢንተርኔት ቤቷ ልጅ የተረዳችውን እንድትነግረኝ ጠየቅኳት፡፡
‹መዋጮው ለአዲሶቹ የሚቀንሰው የቤቱ ዕጣ በቶሎ ስለማይደርሳቸው ነው፡፡ 7 ዓመት መጠበቅ አለባቸው፡፡ አዲሶቹ  በሚያስቀምጡት ብር ነው ለነባሮቹ ቤት የሚሰራው፡፡ ነባሮቹ የዛሬ 5 ዓመት የቤት ባለቤት ይሆናሉ፡፡ ነባሮቹ ልክ ቤታቸው እንደገቡ ደግሞ በሚከፍሉት ብር ለአዲሶቹ ቤት ይሰራላቸዋል፡፡›
‹ነባሮቹ ቤታቸውን ከተረከቡ በኋላ ለምን ይከፍላሉ አስቀመጡ አይደል እንዴ 5 ዓመት ሙሉ?› አላዋቂነቴ ሳይገርማት አልቀረም
‹እንደ ተቀማጩ እኮ 50 ፐርሰንት ነው፡፡ የት ነበርሽ አንቺ ይሄ ሁሉ ሲወራ?›
ምሳ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ቴሌቪዥን ለነባር ተመዝጋቢዎች ፣ ለሴቶች ለመንግስት ሠራተኞች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ሰምቻለሁ፡፡ እንዲህ እያወራን አንድ ሰውዬ መጣ፡፡ ‹እስኪ የኮንደሚኒየም ዕጣ እዩልኝ› አለ፡፡ፊቱ በደስታ በርቷል፡፡
‹አዲስ የኮንደሚኒየም ቤት እጣ አለ እንዴ?› አልኩ መቼም መጠየቄ ካልቀረ የሚሰራ የሚወራውን ሁሉ ልወቅ የሚል ዘመቻ የያዝኩ ይመስላል፡፡
‹በመጨረሻ የወጣው ነዋ›
‹መቼነው እሱ የወጣው? ይቅርታ ከዚህ በፊት ስላልተመዘገብኩ ዕጣ ሲወጣ ጉዳዬ ብዬ አልከታተልም ፡፡› አልኳት፡፡
‹ያኔ ነዋ የምርጫው ሰሞን?›
‹የቱ ምርጫ?›
‹የኢህአዴግ ምርጫ ነዋ! ልክ ምርጫው ሲቀርብ እኮ ነው የወጣው› አለች
‹እኮ ታዲያ እሱ ዕጣ አልቆየም እንዴ?›አልኩና ከጨዋታ ውጪ መሆኔን ለመሸፈን ዕጣው እንዲታይለት የፈለገውን ሰው ወደ ጨዋታው እንዲህ ስል አስገባሁት፡፡
‹አንተ እስከዛሬ እንዴት ዕጣውን ሳታይ ቆየህ?›
‹ሰዎች የኮንደሚኒየም ዕጣ እንደደረሰኝ ነግረውኝ፡፡አላምን ብዬ አይቼው አሁንም በድጋሚ ኢንተርኔት ቤት ቀይሬ ላየው ነው፡፡›
‹እንኳን ደስ ያለህ፡ ግን ለምንድነው ደጋግመህ የምታየው ዕታ ከወጣ በኋላም ስም ይጠፋል?›
‹ሳይሆን እኔ አልተመዘገብኩም ነበራ!›
‹ምን?!›
‹ሙች! ለሴት ቅድሚያ ይሰጣል ብለን ሚስቴ ነበረች የተመዘገበችው፡፡ ሁልጊዜ ዕጣ ሲወጣ የሷን ስም ነው የምንፈልገው፡፡ አሁን እኔን ደረሰህ አሉኝ ስሜ እስከነ አያቴ እስከ አድራሻዬ እኮ ነው ቁልጭ ብሎ የተገኘው፡፡ምንም ስህተት የለበት፡፡›
‹ቢጫዋ ካርድ አለችህ?›
‹የለችኝም፡፡ አልተመዘገብኩም እያልኩሽ?›
‹ሌላ ሰው ተመዝግቦልህ ይሆናል፡፡›
‹ማንም አልተመዘገበልኝ፡፡ ደግሞስ ለሰው መመዝገብ ይቻል ነበር እንዴ?›
‹ታዲያ እንዴት ሊደርስህ ይችላል? ወይ የሆነ የሄድክበት አቋራጭ መንገድ ይኖራል፡፡›
መሀላውን ደረደረ፡፡ እኔ ጭንቅላት ውስጥም እንዲህ እንዲህ እያሉ ጥያቄዎች ተደረደሩ፡፡ ሰዎች የሆነ የሰሙት ነገር ሳይኖር መቼም ስማቸውን ፍለጋ ኢንተርኔት ቤት ለኢንተርኔት ቤት አይንከራተቱም? የኮንደሚኒየም ተመዝጋቢዎች ስም በኢንተርኔት ላይ ይገኛል አይገኝም? ሰዎች ተመዝግበን ስናበቃ ስማችን እየተሰረዘ ጠፋ እያሉ ይጨነቃሉ፡፡ እውነት ነው ውሸት? መቼም ላም ባልዋለበት ኩበት አይለቀምም እሳት በሌለበትም ጭስ የለም፡፡ አንድ ሰው ሳይመዘገብ የኮንደሚኒየም ዕጣ የሚደርሰው እንዴት ባለው ተዓምር ነው? ተመዝግቦ 10 ዓመት ቤት ከመጠበቅና ሳይመዘገቡ ተዓምር ከመጠበቅ የቱ ያዋጣል? እሺ መንግስት ራሴ ሰርቼ ነው የምሰጣችሁ ብሩን ለኔ ስጡኝ ከዛ ዕድሜ ዘመናችሁን ቤት እያላችሁ ጠብቁኝ ማለቱን ይበል የሚሰለፍለት ካገኘ እሰየው፡፡ ግን ሰፋ ያለ የመመዝገቢያ ጊዜ ገደብ መስጠት(ልክ የምርጫ ካርድ እንደመውሰድ ያለ በጠዋት ቤት ለቤት እየዞሩ ‹የመጨረሻው ቀን ቀርቧል› እያሉ እንደሚቀሰቅሱት ዓይነት)፣ከምር ቤት የቸገረውን ለይቶ መስጠት፣መሬት ሰጥቶ እንደፈለጋችሁ ስሩ ማለት አይችልም ነበር?
‹አንቺ ግን እንደባለፈው እንዳያመልጥሽ አሁን ተመዝገቢ፡፡በኋላ እንዳይቆጭሽ፡፡› አለችኝ ስወጣ ጠብቃ

እኔ ለራሴ ገና ጥያቄ ላይ ነኝ፡፡ ብር ብሎ ተነስቶ እንደሚሰለፍ ህዝብ ብዙ ነገር አልገባኝም፡፡ ጥያቄ - ጥያቄ  -ጥያቄ ፡፡ ጥያቄ አያልቅም፡፡



ጸሃፌ ተውኔት መዓዛ ወርቁን በሸገር የአልጋ በአልጋ ተከታታይ ድራማና በህይወት መሰናዶ ድራማ ደራሲነታቸው እናስታውሳቸዋለን፡፡ አሁን እየታየ የሚገኝ ዝነኞቹ የተሰኘ ቴአትርም አላቸው፡፡ አስተያየት ካላችሁ በፌስቡክ አድራሻቸው በኩል በhttps://www.facebook.com/meaza.worku.39 ሊያገኙዋቸው ይችላሉ፡፡

Saturday, May 25, 2013

የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ኢንተርኔት ፫

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የሃገራችን ቋንቋዎች በተለይም አማርኛ ለቀጣይ ዘመን የሚሆነውን ዝግጅት ከአሁኑ መጀመር እንዳለበት ሳወራችሁ ቆይቻለሁ፡፡ ይህንንም የሚረዳ አንድ አይነት እንቅስቃሴ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅትም እያደረግን ነው፡፡ አሁንም ይህንን ሃሳብ ለማገዝ የሚፈልግ በኢሜል አድራሻዬ feruzj30@gmail.com  ይላክልኝ፡፡ ጽሁፉን አንብባችሁ የተቻላችሁን ለማድረግ ቃል የገባችሁልኝን ኢትዮጵያውያን አመሰግናለሁ፡፡ በተለይም አቶ ሞረሽ ሻሎምን ከደቡብ ኮሪያ፣ የኢንተርኔት አጠቃቀም መመሪያ በአማርኛ የተሰኘውን መጽኃፍ ተባባሪ ደራሲ አቶ ወንደሰን አሰፋ፣ የሶፍትዌር ኢንጂነሩን አቶ ዮናስንና ለኖኪያ ስልኮች የሚሆን የአማርኛ ሶፍትዌር የሰሩት አቶ ነቢዩን በጣም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
የአማርኛና ሌሎች ሃገራችን ቋንቋዎች ለ21ኛው ክፍለዘመን የበቁ ማድረግ የሚጀምረው ቋንቋዎቹ በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ዲጂታል ኣለም ውስጥ ያላቸውን ቦታ በማሳደግ ይሆናል፡፡ ለሺ ዓመታ ቆዩ ቋንቋዎች በሶስት ትውልድ ጊዜ ለመጥፋት ሲቃረቡ አይተናልና፡፡  ወደ ቤተመጻህፍት መሄድ ሳያስፈልግ፣ በጣም አዲስና ወዲያው ወዲው የሚታደስ የእውቀት ቋት ቢኖርና ማንም ሰው ገብቶ ሊያገኝው ቢችል ሊፈጠር የሚችለውን የእውቀት ፍንዳታ ማሰብ ቀላል ነው፡፡ በኢኮኖሚ በለጸገ፣ በዲሞክራሲ ታነጸና ተራማጅ ሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር መቼም እንደ ትምህርትና እውቀት ሚሆን ነገር የለም፡፡ቤትምህርት ቤቱ ሚገኝ በስርዓት የተዋቀረ ትምህርት ብቻ ደግሞ ይህንን መሰለ ለውጥ ሊያስከትል አይችልም፡፡ በመንግስት መዝገብ ቤቶች፣ በቤተ መዘክርና ቤተ መጻህፍት፣ በሚዩዚሞች፣ በየቤቱ ያለና በሰው ዘንድ የሚገኝ እውቀት የሌለው ካለው እንዲያገኝ፣ እውቀት ለተወሰኑ ብቻ የተሰጠ፣  የታደሉት ብቻ የሚጠቀሙበት ሃብት መሆኑ እንዲያበቃ መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ሁሉ መረጃ ከያለበት ተሰብስቦ ሁሉም በቀላሉ ሊያገኘው በሚችል ቦታ መቀመጥ አለበት፡፡ እውቀት ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መብቶች አንዱ ነው፡፡ ቤንሻንጉል ገጠር ያለ፣ አፋር ከግመሎቹ ጋር የሚውልና አዲስ አበባ የሚኖር  እኩል ተፈጥሯዊ የእውቀት ጥማት አላቸው፡፡ በመሆኑም እድሉ ያለን ዜጎች፣ ሃላፊነቱን የሰጠነው መንግስትና ሌሎች ሚመለከታቸው ወገኖች ግዴታችንን መወጣት አለብን፡፡

ቢሮክራሲ ባለተጫነው ሁኔታ ሰዎች ባሉበት ሃገር ሆነው ለዚህ የእውቀት ቋት ማበርከት ቢችሉ፣ ይህንን የሚያስተባብረውም አካል የአርትኦት ስራውን ከቋንቋ፣ ከቁጥሮችና ከማጣቀሻዎች አንጻር ቢያከናውን፣ የአይቲ ባለሙያዎች በተለያዩ መልኩ በስልክ፣ በኮምፒውተር ወይንም በማንኛውም ኤሌክትሮኒካዊ  የመገናኛ ዘዴዎች ሁሉም ባመቸው ወቅትና ቦታ እንዲታይና እንዲገኝ ቢደረግ፣ ተጠቃሚውም ከምንም አይነት ክፍያ ነጻ በሆነ ሁኔታ አገልግሎቱን ቢያገኝ የፕሮጀክቱ ዋና መነሻ ምክንያቶች ናቸው፡፡ከአማርኛም በተጨማሪ በሌሎች የሃገራችን ቋንቋዎች ይህ የእውቀት ቋትን ማግኘት ቢቻል ቅድም ያወራናችን እውቀት የሁሉም ዜጋ ተፈጥሯዊም፣ ህጋዊም እንዲሁም ሞራላዊም መብት ነው ያልኩትን ማስፈጸም ይቻላል፡፡ ይህንን ሁሉ ለማድረግ ገንዘቡም፣ እውቀቱም ፍላጎቱም በኛው በዚህች ሃገር ዜጎች ይገኛል፡፡ ምናልባት የፈቃደኝነት እና የግንዛቤ ማጣት ካልሆነ በቀር፡፡ መንግስትም ቢሆን የዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ኢትዮጵያ ለማኖር ባህልን፣ ቋንቋንና ታሪክን ዘመን እንዲሻገሩ ማድረግ ሃፊነት አለበት፡፡ የክፍለ ሃገር ልጅ እንደመሆኔ በተለይ በቤተ መጻህፍትና ቤተ መዘክር የሚገኙ መረጃዎችን ለማግኘት አዲስ አበባ መኖር የግድ መሆኑን ሳስበው ያሳዝነኛል፡፡ የተከማቸው መጽሃፍ፣ ማይክሮ ፊልምና ሌላውም ሁሉ አዲስ አበቤዎች መሆኑ ይገርመኛል፡፡ ነገር ግን በየደረስኩበት ሁሉ ይህንን የሃገሬን እውቀት ባገኝ ለኔ በግሌ ከማገኘው ጥቅም በለጠ ለሃገር ይሰጣል፡፡

ጸሃፊው ፌሩዝ ጀማል በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 ሬዲዮ በ IT, ድምጽ ላይብረሪና ፕሮግራም ትራፊክ ሃላፊነት ይሰራሉ፡፡ ጸሃፊውን ለማግኘት በፌስ ቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/feraj?ref=tn_tnmn  በኢሜላቸው feruzj30@gmail.com መጠቀም ይቻላል፡፡